ፓሪስ ከኦሎምፒኩ በፊት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ደምቃ ዋለች

ፓሪስ ከኦሎምፒኩ በፊት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ደምቃ ዋለች

በፓሪስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ድጋፍ ከፍተኛ ነበር

ፓሪስ – 09-04-2024

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በድል ያሸበረቁበት ፣ ለኢትዮጵያም አስደሳች ውጤቶች አስገራሚ ታሪኮች የተመዘገቡበት መነሻውን ከውቧ የፓሪስ ሻንዜሊዜ ጎዳና ያደረገው 47ኛው የፓሪስ ማራቶን ባለፈው እሁድ ተካሂዷል። ከ 20 በላይ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ፣ የኬንያ ፣ የፈረንሳይ እና እንዲሁም ከስዊዘርላንድ የተውጣጡ አዋቂ ሴት እና ወንድ አትሌቶችን ጨምሮ ወደ 54 ሺ የሚጠጉ ተወዳዳሪዎችም ተካፋይ ሆነውበታል።

በዚሁ የፓሪስ ማራቶን በወንዶቹ የ 42ኪሎ ሜትሩን ርቀት አትሌት ሙሉጌታ አሰፋ ኡማ በ2ሰአት ከ05 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በሆነ ሰአት በቀዳሚነት በመግባት ባለ ድል ሆኗል ኢትዮጵያም በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን ላይ ለሶስት ተከታታይ አመታት በወንዶቹ ድልን ስታስመዘግብ በፓሪስ ማራቶን የ47 አመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ መሆኑም ታውቋል።

በሴቶቹ ርቀት ተወዳዳሪ ከነበሩት አትሌቶች መስታወት ፍቅር በ 2ሰአት ከ20ደቂቃ ከ45 ሰከንድ አሸናፊ ስትሆን ሌላኛዋን ኢትዮጵያዊት አትሌት እናትነሽ ጥሩ ሰውን በሁለተኛ ነት አስከትላም በመግባት ጭምር ነበር
ሁለቱም ባለድል የሆኑ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶችም የመጀመሪያውን የማራቶን ድላቸውን ያስመዘገቡበት በመሆንም አዲስ ታሪክ ተፅፎበታል።

team ethiopia 2024

ምንም እንኳን ከእሁዱ ማራቶን ቀደም ብሎ የአሸናፊነቱን ቅድመ ግምት እ.ኤ.አ የ2020 እንዲሁም 2023 የፓሪስ ማራቶን አሸናፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ዴሶ ገለሚስ እና አበጀ አያና እንዲሁም የ2021 አሸናፊ ኬንያዊው ኤሊሻ ሮቲች ግምት ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም አትሌት ሙሉጌታ ግን ግምቶቹን ወደ ኋላ በማስቀረት ከ30 ኪሎ ሜትር በኋላ ወደፊት በመውጣት በተለይም ደግሞ ከ 40ኪሎ ሜትር በኋላ ቀሪዎችን 2 ኪሎ ሜትሮች ፍጥነቱን በመጨመር ከቅርብ ርቀት ሲፎካከሩት ከነበሩት ሁለቱ ኬንያዊያን አትሌቶች ቲተስ ኪፕሩቶ እና ከኤሊሻ ሮቲሽ መሀል ተስፈንጥሮ በመውጣት በመጨረሻም የአሸናፊነትን የድል ማብሰሪያ ገመዱን በደረቱ በጥሶ በመግባት ድልን ተቀናጅቷል ።
ለፓሪስ ማራቶንም ከረጅም ጠንካራ ልምምድ በኋላ ፓሪስ ላይ የመጀመሪያውን የማራቶን ድሉን በማዝመዝገቡም ከፍተኛ ደስታ የተሰማው መሆኑንከውድድሩ በኋላ ሙሉጌታ ተናግሯል።

በሴቶቹ ርቀት ኬንያዊይቷ የረጅም ርቀት የኦሎንምፒክ እና የአለም ሻምፒዮናዋ ሺቪያን ቼሩየት ከ3 አመት ቆይታ በኋላ ወደ ውድድር መመለሷን ተከትሎ በፓሪሱ ማራቶን ላይ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷት የነበረች አትሌት ብትሆንም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መስታወት ፍቅር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሆነው የፓሪስ ማራቶን ተሳትፎዋ አሸናፊ በመሆን አስደናቂ ድልን ለሀገሯ አስመዝግባለች ። ሙሉ ማራቶን ስትሮጥ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑን ለቲም ኢትዮጵያ 2024 ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የገለፀችው አትሌት መስታወት ውድድሩ ላይ የገጠሟት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ሆኑ ኬንያዊቷ ቪቪያን መኖሯ ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን ውድድሯን እንድታሸንፍ የረዳት መሆኑን ገልፃለች።

እንዲሁም በፓሪስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በውድድር ስፍራው ላይ በመገኘት ለአትሌቶች ላደረጉላቸው ድጋፍ እና ማበረታታትም አትሌቷ ምስጋናዋን አቅርባለች ።

team ethiopia 2024

በዚሁ በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን ውድድር በሴቶቹ ቪቪያን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን ተከትላ 3ኛ ሆና ውድድሯን ስታጠናቅቅ ከ5 እስከ 8 ያለውን ደረጃ ኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች ተቆጣጥረውታል ።

በመጨረሻም በዚሁ በፓሪስ ማራቶን ውድድር ላይ በመነሻ እና በውድድሩ መጨረሻ ስፍራዎች ላይ በመታደም ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሞቅ ያለ ድጋፋቸውን በፓሪስ እና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሲሰጡ ተስተውለዋል ።

በተመሳሳይም በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ላይ ተሳታፊ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ይሄን መሰሉን ድጋፍ እና ማበረታታት አጠናክረው ለመስጠት እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

#ቲም ኢትዮጵያ 2024 ፓሪስ ሚዲያ እና ኮሙኒዩኬሽን💫

በፓሪስ ኦሎምፒክ ምንም የሽብር ስጋት እንደሌለ የፈረንሳይ  የስፖርት  ሚንስትር  ገለፁ

በፓሪስ ኦሎምፒክ ምንም የሽብር ስጋት እንደሌለ የፈረንሳይ የስፖርት ሚንስትር ገለፁ

ከ ፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ዝግጅት ጋር በተያያዘ በሀገራቸው ምንም የሽብር ስጋት እንደሌለ የፈረንሳይየስፖርት ሚንስትር የሆኑት አሜሊ ኦውዴያ፡ካስቴራ ሰሞኑን ፍራንስ 2 በሚባለዉ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ አረጋግጠዋል ።
አሜሊ ኦውዴያ ካስቴራ ስለ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የደህንነት ስጋት እንደሌለ ቢገልፁም ነገሮችን ለማረጋጋት እስከ ሰኔ 12 ድረስ የመክፈቻዉን እለት ትርኢት የሚያቀርቡት በሙሉ እይታ ልምምዱን በቦታዉ ላይ እንደማያደርጉ እና ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ተከትሎ በሴይን ላይ የሚካሄደው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት አዘጋጆቹ እየሠሩበት ያለው “ማዕከላዊ ዕቅድ” ሆኖ እንደቀጠለም አክለዉ ገልፀዋል ።
ከአሸባሪዎች ስጋት አስፈላጊውን ሁሉ የሚመለከታቸው አካላት በጥንቃቄ እየተከታተሉ መሆኑንም ሚኒስትሯ አስረድተዉ ።

ይህ የተፈራዉ ሽብር ቢያጋጥም ሌላ ሁለተኛ አማራጭ እንዳለ ለተጠየቁት መልስ የሰጡት አሜሊ ኦውዴያ “እስከሚያዉቁት ሀገራቸዉን በዚህ በኦሎምፒክ ዝግጅት ከሌላዉ ጊዜ በተለየ የሽብር ስጋት የለም” ሲሉ አረጋግጠዋል።
በርግጥ የፈረንሣይ መንግሥት ከመጋቢት 22 በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው የኮንሰርት አዳራሽ ላይ ከተፈጸመው የሽብር ጥቃት በኋላ ሀገራቸዉ ፈረንሳይ የደኅንነት ዕቅዷን ወደ ከፍተኛው ደረጃ ከፍ ለማድረግ መወሰኗን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በእ.ኤ.አ ሐምሌ 26 2024 ለሚካሄደው የመክፈቻ ስነ ስርዓት እቅድ ሁለት እንደሌለ በድጋሚ ለተጠየቁት ሚኒስትሯ ሲመልሱ “ይህ በሴን ወንዝ ላይ የሚደረገው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የእኛ ማዕከላዊ እቅዳችን ነው ። መከበር ያለበትም የታቀደዉ ቦታ ላይ ነዉ።
የቴክኒክ ሙከራዎች እና ሌሎችም ልምምዶች ከታቀደዉ ቀን ለዉጥ እንደተደረገባቸዉም ከሳምንታት በፊት አሳዉቀናል” ሲሉ ለጥያቄዎቹ መደምደሚያ ሰጥተዋል።
ቲም ኢትዮጵያ 2024 ፓሪስ
#ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን 💫

በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን ወድድር  ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ቅድመ ግምት አግኘተዋል

በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን ወድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ቅድመ ግምት አግኘተዋል

በዚህ ውድድር ላይም መኩነት አየነው ( 2 ሰአት ከ 04 ደቂቃ ከ 46 ሴኮንድ እኤአ በ2020 በስፔን የሲቪል ማራቶን አሸናፊ ) ፣ ባዘዘው አስማረ (2 ሰአት ከ 04 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ የ2022 የአምሰተርዳም ማራቶን አሸናፊ ) በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መሆናቸው ሲታወቅ የአምናው የፓሪስ ማራቶን አሸናፊ አትሌት አበጀ አያና (2 ሰአት ከ 04 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ) ከዚህ ቀደም በተከታታይ በዚሁ የፓሪስ ማራቶን ውድድር ላይ አሸናፊ እንደነበሩት ኬንያዊዉ ፖል ሎንያንጋታ (እኤአ 2017 እና 2018) እንዲሁም እንደ ብሪታንያዊዉ ሯጭ ስቲቭ ብራስ እ.ኤ.አ 1989 እና 1990 ለሁለተኛ ጊዜ ድሉን ፓሪስ ላይ ለማስመዝገብ የሚችልበት ከፍተኛ እድል እንዳለው ተገምቷል :: ሆኖም ግን በዘንድሮው ውድድር ላይ ከ2ሰእት ከ05 ደቂቃ በታች ያላቸው ወደ 7 የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዉያን አትሌቶች ተካፋይ በመሆናቸው ብርቱ ውድድር ሊገጥመው ይችላልም ተብሏል ።

እ.ኤ.አ የ 2021 የፓሪስ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊው ኤሊሽ ሮቲች ወደ ሁለት አመት ገደማ በጉዳት ምክንያት ከውድድር እርቆ ቢቆይም በእሁዱ የፓሪስ ማራቶን ቅድሚያ ያሻናፊነቱን ግምት ከወሰዱት አትሌቶች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቋል።
ሆኖም ከሀገሩ ልጆች ሂላሪ ኪሳምቡ ፣ በሪሚን ኪፓኮሪር ፣ ቲተስ ኪፕሩቶ እና ከኢትዮጵያን አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር ሊገጥመው እንደሚችል ተገምቷል ።

በተመሳሳይም በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን በሴቶች ውድድር ኢትዮጵያዊያኑ እና ኬንያዉያኑ አትሌቶች ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ሲሆን ለዚህም ደግሞ ባለፉት 15 አመት የፓሪስ ማራቶን ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያዊያኑ ሴት አትሌቶች ሰባት ጊዜ የአሸናፊነት ክብርን ሲቀናጁ ኬንያዉያኑ ሴት አትሌቶች ደግሞ 8 ስምንት ጊዜ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ቅድመ የአሸናፊነት ግምቱ በሁለቱ ሀገራት አትሌቶች መካከል እንደሚሆን ተጠብቋል ።

እ.ኤ.አ 2019 የፖሪስ ማራቶን አሸናፊ አትሌት ገለቴ ቡርቃ ዳግም ለሌላ ድል ወደ ፓሪስ ጎዳና መመለሷ ታውቋል ። ሌላኛዋ አትሌት ብዙነሽ ጌታቸው ስትሆን ከዚህ ቀደምም እኤአ በ2019 በፍራንክ ፈርት አሸናፊ ነበረች ። በተጨማሪም ራህማ ቱሳ ፣ እታገና ወልዱ ፣ እኤአ የ2023 የ ኦሳካ ጃፓን አሸናፊ ሄቨን ሀይሉ ፣ መስታውት ፍቅሬ እና እናትነሽ ጥሩሰው በፓሪስ ማራቶን ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ።

በሌላም በኩል የኢትዮጵያውያን የቅርብ ተፎካካሪ ከሆኑት አትሌቶች በቀዳሚነት የምትጠቀሰዉ በሪዬ ኦሎምፒክ በ5000 ሜትር ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እና በተለያዩ አለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ አሸናፊ የነበረችው ኬንያዊቷ አትሌት ቪቪያን ቼሩየት በወቅቱ ዉድድር የአሸናፊነት ክብርን ልታገኝ እንደምትችል ብትገመትም ከቫሌንሽያ 2019 የማራቶን ውድድር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማራቶን ውድድር መመለሷ መሆኑን ተከትሎ ከሀገሯ ልጆች ሆነ ከኢትዮጵያዉያኑ አትሌቶች በኩል ብርቱ ውድድር ሊያጋጥማት እንደሚችል ተገምቷል ።

የፓሪስ ማራቶን የተወዳዳሪዎች የ ፓሪስ ዋና ዋና ጎዳናዎች የሆኑትን እንደ ባስቲ አደባባይ ፣ እንደ ኤፈል ታወር ፣ ኮንኮርድ የመሳሰሉ ቦታዎችን አቋርጠው የሚያልፉበት ነው መነሻውም በ አለማችን በሚታወቀዉ ትልቁ ጎዳና ሻንዜሊዜ ላይ ሲሆን እንደ በፓሪስ እና አካባቢዋ ሰአት አቆጣጠር ከጥዋቱ 7 ሰዐት ከ 59 መሆኑ ሲታወቅ የአዋቂ ወንዶች ውድድር መነሻ ሰአት ደግሞ 8 ሰዐት ከ15 ደቂቃ መሆኑ ታውቋል ።

በተያያዘም በፓሪስ እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን ላይ ተካፋይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊ አትሌቶችን ለመደገፍ እና ለማበረታታት ብሎም እንዲሁም በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ተሳታፊ ለሚሆኑ አትሌቶችም በተመሳሳይ መልኩ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ለመግለፅ የሚያስችል ዝግጅት ያደረጉ መሆናቸው ታውቋል ።

በእለቱ የውድድሩ መነሻ ስፍራ ከሆነው ሻንዜሊዜ ጎዳና እና የውድድሩ ፍፃሜ በሚደረግበት የፎሽ ጎዳና እንዲሁም አትሌቶች በሚያልፉባቸዉ ዋና ዋና የፓሪስ ጎዳናዎች ላይ በመሰባሰብ ድጋፋቸውን በመስጠት ፓሪስ በኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ድል ሆነ በኢትዮጵያውያኑ ድጋፍ ደምቃ እንድትውል የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ከቲም ኢትዮጵያ2024 ፓሪስ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ቲም ኢትዮጵያ 2024 ፓሪስ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን 💫