በፓሪስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ድጋፍ ከፍተኛ ነበር
ፓሪስ – 09-04-2024
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በድል ያሸበረቁበት ፣ ለኢትዮጵያም አስደሳች ውጤቶች አስገራሚ ታሪኮች የተመዘገቡበት መነሻውን ከውቧ የፓሪስ ሻንዜሊዜ ጎዳና ያደረገው 47ኛው የፓሪስ ማራቶን ባለፈው እሁድ ተካሂዷል። ከ 20 በላይ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ፣ የኬንያ ፣ የፈረንሳይ እና እንዲሁም ከስዊዘርላንድ የተውጣጡ አዋቂ ሴት እና ወንድ አትሌቶችን ጨምሮ ወደ 54 ሺ የሚጠጉ ተወዳዳሪዎችም ተካፋይ ሆነውበታል።
በዚሁ የፓሪስ ማራቶን በወንዶቹ የ 42ኪሎ ሜትሩን ርቀት አትሌት ሙሉጌታ አሰፋ ኡማ በ2ሰአት ከ05 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በሆነ ሰአት በቀዳሚነት በመግባት ባለ ድል ሆኗል ኢትዮጵያም በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን ላይ ለሶስት ተከታታይ አመታት በወንዶቹ ድልን ስታስመዘግብ በፓሪስ ማራቶን የ47 አመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ መሆኑም ታውቋል።
በሴቶቹ ርቀት ተወዳዳሪ ከነበሩት አትሌቶች መስታወት ፍቅር በ 2ሰአት ከ20ደቂቃ ከ45 ሰከንድ አሸናፊ ስትሆን ሌላኛዋን ኢትዮጵያዊት አትሌት እናትነሽ ጥሩ ሰውን በሁለተኛ ነት አስከትላም በመግባት ጭምር ነበር
ሁለቱም ባለድል የሆኑ ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶችም የመጀመሪያውን የማራቶን ድላቸውን ያስመዘገቡበት በመሆንም አዲስ ታሪክ ተፅፎበታል።
ምንም እንኳን ከእሁዱ ማራቶን ቀደም ብሎ የአሸናፊነቱን ቅድመ ግምት እ.ኤ.አ የ2020 እንዲሁም 2023 የፓሪስ ማራቶን አሸናፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ዴሶ ገለሚስ እና አበጀ አያና እንዲሁም የ2021 አሸናፊ ኬንያዊው ኤሊሻ ሮቲች ግምት ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም አትሌት ሙሉጌታ ግን ግምቶቹን ወደ ኋላ በማስቀረት ከ30 ኪሎ ሜትር በኋላ ወደፊት በመውጣት በተለይም ደግሞ ከ 40ኪሎ ሜትር በኋላ ቀሪዎችን 2 ኪሎ ሜትሮች ፍጥነቱን በመጨመር ከቅርብ ርቀት ሲፎካከሩት ከነበሩት ሁለቱ ኬንያዊያን አትሌቶች ቲተስ ኪፕሩቶ እና ከኤሊሻ ሮቲሽ መሀል ተስፈንጥሮ በመውጣት በመጨረሻም የአሸናፊነትን የድል ማብሰሪያ ገመዱን በደረቱ በጥሶ በመግባት ድልን ተቀናጅቷል ።
ለፓሪስ ማራቶንም ከረጅም ጠንካራ ልምምድ በኋላ ፓሪስ ላይ የመጀመሪያውን የማራቶን ድሉን በማዝመዝገቡም ከፍተኛ ደስታ የተሰማው መሆኑንከውድድሩ በኋላ ሙሉጌታ ተናግሯል።
በሴቶቹ ርቀት ኬንያዊይቷ የረጅም ርቀት የኦሎንምፒክ እና የአለም ሻምፒዮናዋ ሺቪያን ቼሩየት ከ3 አመት ቆይታ በኋላ ወደ ውድድር መመለሷን ተከትሎ በፓሪሱ ማራቶን ላይ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷት የነበረች አትሌት ብትሆንም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መስታወት ፍቅር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሆነው የፓሪስ ማራቶን ተሳትፎዋ አሸናፊ በመሆን አስደናቂ ድልን ለሀገሯ አስመዝግባለች ። ሙሉ ማራቶን ስትሮጥ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑን ለቲም ኢትዮጵያ 2024 ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የገለፀችው አትሌት መስታወት ውድድሩ ላይ የገጠሟት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ሆኑ ኬንያዊቷ ቪቪያን መኖሯ ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን ውድድሯን እንድታሸንፍ የረዳት መሆኑን ገልፃለች።
እንዲሁም በፓሪስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በውድድር ስፍራው ላይ በመገኘት ለአትሌቶች ላደረጉላቸው ድጋፍ እና ማበረታታትም አትሌቷ ምስጋናዋን አቅርባለች ።
በዚሁ በዘንድሮው የፓሪስ ማራቶን ውድድር በሴቶቹ ቪቪያን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን ተከትላ 3ኛ ሆና ውድድሯን ስታጠናቅቅ ከ5 እስከ 8 ያለውን ደረጃ ኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች ተቆጣጥረውታል ።
በመጨረሻም በዚሁ በፓሪስ ማራቶን ውድድር ላይ በመነሻ እና በውድድሩ መጨረሻ ስፍራዎች ላይ በመታደም ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሞቅ ያለ ድጋፋቸውን በፓሪስ እና በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሲሰጡ ተስተውለዋል ።
በተመሳሳይም በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ላይ ተሳታፊ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ይሄን መሰሉን ድጋፍ እና ማበረታታት አጠናክረው ለመስጠት እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
#ቲም ኢትዮጵያ 2024 ፓሪስ ሚዲያ እና ኮሙኒዩኬሽን💫